መንግሥት እየደጎመ ያስቀጠለው የስፖርት ዘርፍ ራሱን ችሎ እንዲቆም ፈንድ ሊቋቋምለት ነው
EthiopianreporterFeb 14, 2026Read original
ከ90 በመቶ በላይ በመንግሥት በጀት እየተደገፈ ቀጥሏል የተባለው የስፖርት ዘርፍን ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ድጋፍ ያላቅቀዋል የተባለ የስፖርት ፈንድ ሊቋቋም መሆኑ ተገለጸ፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች የስፖርት ልማትና አስተዳደር አዋጅን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ የባህልና የስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ማብራሪያ ሲሰጡ ነው ይህ የተነገረው፡፡
በመድረኩ የተገኙት አንድ የሚኒስቴሩ ኃላፊ በሰጡት ማብራሪያ፣ አዋጭ ሥልት ተቀይሶ ስፖርት ራሱ ን የቻለ ፈንድ ተቋቁሞለት ከመንግሥት እንዲላቀቅ በረቂቅ አዋጁ መካተቱን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ የስፖርት ፈንድ በማሳያነት የተገለጸ ሲሆን፣ ፈንዱ ከተቋቋመ ፋይናንስ በማፈላለግ ውድድሮችን እየመራ ስፖርቱን ከመንግሥት በማላቀቅ ራሱን ችሎ ተቋቁሞ የስፖርት ማኅበራትን እንዲመራ ታስቧል ብለዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ እንደተብራራው የፌዴራል ስፖርት ልማት ፈንድ እንደሚቋቋም፣ ድጋፉንና ፈንዱ የሚተዳደርበትን በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደሚያወጣ ተደንግጓል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ አቶ በላቸው ድሪባ፣ ኢትዮጵያ ለአትሌቶች [ለእግር ኳስ ተጫዋቾች] በጣም ከፍ ያለ ደመወዝ በመክፈል እንደምትታወቅ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እጅግ ከፍተኛ ደመወዝ ነው የምንከፍለው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚባሉ ከ90 በመቶ በላይ ክለቦች የሚተዳደሩት በመንግሥት ፈንድ ነው፡፡ መንግሥት ለስፖርት ቢሊዮን ብሮችን እያወጣ፤›› ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ክፍያ በመጠየቃቸው ምክንያት የውጭ አገር ስፖርተኞች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ በአነስተኛ ዶላር እየተቀጠሩ በመሆናቸው በሰው ሀብት ልማት ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ ማሳረፉን፣ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ኢትዮጵያውያን መጫወት በሚችሉበ ት ቦታ ሁሉ የውጭ አገር ተጫዋቾች እንዲገቡ መፈቀድ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡
የአትሌቲክስ ዘርፉ በሕግና በሥርዓት እንደማይመራ የተገለጸ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የስፖርት ሁነቶችን ማን ከየት ፈቃድ ወስዶ እንዳዘጋጃቸው አይታወቅም ብለዋል፡፡ ከዚያም አልፎ የሃይማኖት ተቋማት ጭምር የስፖርት ሁነት ሲያዘጋጁ እየታየ ነው ተብሏል፡፡
ስፖርት ኢትዮጵያ አለኝ ብላ ከምታስባቸው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ አገልግሎቶች አንዱ ነው ያሉት የሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለኢንቨስትመንትና ለሌሎች ጉዳዮች እየተወሰዱ በመሆናቸው እንዲከለከሉና እንዲታጠሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ለስፖርት አመራርነት ለመመረጥ መደለያ መስጠት፣ የስፖርት ውድድር ወይም ኩነትን ለማካሄድ ጉቦ ለመስጠትና ለመቀበል፣ ድርድር ሲያደርግ የተገኘ ከአሥር ዓመት የማያንስ ፅኑ እስራት ቅጣት የሚጥል ሲሆን፣ የምክር ቤቱ የሕግ ከፍል ባቀረበው ጥያቄ መደለያ ለሰዎች መስጠት በዚህ ልክ ሊያስቀጣ ይችላል ወይ በማለት ጠይቋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ አበረታች ቅመም ተጠቅሞ የተገኘ አትሌትን ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስርና ከ100 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት፣ እንዲሁም ለአትሌቱ አበረታች ቅመም እንዲጠቀም ያዘዘና የሰጠ እንደ ጉዳዩ ሁኔታ እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ እስራትና እስከ 500 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣትን ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን የሕግ ክፍሉ የሰጪው ቅጣት ከተጠቃሚው የበለጠ እንዴት ሊከብድ ቻለ ሲልም ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ቅመሙን ያዘዘው፣ የሰጠው፣ እንዲሁም በሕክምና አስፈላጊነቱን ያመነበት ተቋም ወይም የተፈጥሮ ሰው ከሆነ የቅጣቱ አወሳሰን ትክክል አለመሆኑን ማብራሪያ የጠየቀ ሲሆን፣ ውሳኔውም ከወንጀል ሕጉ ጋር የተጣጣመ መሆኑ በግልጽ እንዲብራራ ጠይቋል፡፡
አበረታች ቅመም ላይ የተጣለው ቅጣት በአትሌቶች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ቀላል ባለመሆኑና ስፖርቱንም ወደፊት ሊያሸጋግረውም ባለመቻሉ ነው ያሉት፣ የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፈንቴ ገዛኸኝ ናቸው፡፡
ከጊዜ በኋላ ከጥቅም ውጪ የሚሆኑ አትሌቶች እየበዙ መሆናቸውን ገልጸው፣ በሥልጠና ወቅት እየታየ ያለውም በስፖርት ውስጥ ለመቆየት አበረታች ቅመም መጠቀም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በረቂቁ የቀረበው ድንጋጌ ከወንጀል ሕጉ በተሻለ ጠንከር ብሎ እንዲወሰን መታሰቡን ጠቅሰው፣ አሁንም ያንሳል ሲሉ አስረድተዋል፡፡